የካ ክፍለ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ

Yeka Subcity on Mapየየካ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ በኩል ይገኛል፡፡ የክፍለ ከተማው ስፋት 85.98 ኪሎ ሜትር ካሬ ሲሆን በኪሎ ሜትር ካሬ የሰፈረው ሰው 4,284.9 ነው፡፡ የክፍለ ከተማው የህዝብ ብዛት 368,418 ነው፡፡  የክፍለ ከተማው አስተዳደር በ22 ማዞሪያ አከባቢ ከሌክስ ፕላዛ ህንፃ ቀጥሎ ይገኛል፡፡  ስልክ ቁጥሩ 01116 51 55 89 ሲሆን የፋክስ ቁጥሩ ደግሞ 0116 62 06 39 ነው፡፡  ፖስታ ሳጥን ቁጥሩም 110104 ነው፡፡

ክፍለ ከተማው 347 ሴት፣ 200 ወንድ በድምሩ 547 ቋሚ ሰራተኞች ሲኖሩት 24 በተወሰነ (Contract) የተቀጠሩ ሰራተኞች አሉት፡፡  በበጀት ዓመቱ 337 ሚሊዮን 750 ሺህ 165 ብር ከ29 ሳንቲም የተበጀተለት ሲሆን 672 ሚሊዮን 072 ሺህ 002 ብር ከ85 ሳንቲም ብር የካፒታል ወጪ አድርጓል፡፡

በክፍለ ከተማው አራት የመንግሥት፣ 137 የግል እና 15 የተቋም አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶች አሉት፡፡  15 የመንግሥትና 587 የግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል::  እንዲሁም ስድስት የመንግስትና አስር የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉት፡፡  በተመሳሳይ አምስት የቴክኒክና ሙያና 21 የተቋም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች አሉበት፡፡  አንድ የመንግሥት እና ስድስት 6 የግል ኮሌጀች ሲኖሩበት ሁለት ዩንቨርስቲዎችም ይገኙበታል፡፡

በክፍለ ከተማው 49 የተቋም መለስተኛ ክሊኒኮች፣ 25 የተቋም ከፍተኛ ክሊኒኮች፤ ሁለት የመንግሥት ሆስፒታሎች እና አራት የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች አሉበት፡፡

በክፍለ ከተማው ወረዳ አምስት የሚገኙት የእንግሊዝ፣ የራሺያ እና የኬኒያ ኢምባሲዎች ይገኙበታል፡፡  ወረዳ ሦስት የሚገኙት የጀርመንና የጣሊያን ኢምባሲዎችም በዚሁ ክፍለ ከተማ ይገኛሉ፡፡  በወረዳ አንድ የሚገኘው የፈረንሳይ፣ ወረዳ ዘጠኝ የሚገኘው የእስራኤል እና የቤልጀም ኢምባሲዎችም ይገኛሉ፡፡

በክፍለ ከተማው በስሩ በሚኙት ወረዳዎች 24 ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡  እንዲሁም የሰራ መናፈሻ በወረዳ 12፣ የሚሊኒየም መዝናኛ ፖርክ በወረዳ አስር፣ የየካ መዝናኛ ቦታ በወረዳ አምስት እና የፈረንሳይ መዝናኛ ቦታ በወረዳ ሦስት በዚሁ ክፍለ ከተማ  ይገኛሉ፡፡

በክፍለ ከተማው የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ እና ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ይገኙበታል፡፡  የአዲስ አበባ ትራፊክ ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እና የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢኒስቲቲዩትም በዚሁ የሚገኙ ናቸው፡፡ ክፍለ ከተማው 15 የኦርቶዶክስ፣ ስምንት የእስልምና እና 16 የፕሮቴስታንት ሐይማኖቶች ተቋማት የሚገኙበት ነው፡፡