ሙዝየሞች ሙዝየሞች

:: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም

:: የእንጦጦ ሙዚየም

:: የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም

:: ዚኦሎጂካል የተፈጥሮ ታሪክ ሙዝየም (ZNHM)

:: ባዕታ ሙዝየም

:: ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሙዝየም

:: አዲስ አበባ ሙዝየም

:: የቀድሞው የኢትዩጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ቋሚ አውደ ራዕይ

:: ብርሃን ማዕከል ሙዝየም

:: ዳግማዊ ምኒሊክ ሙዚየም

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም

National Museumበኢትዮጵያ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ እንቅስቃሴ የተጀመረው ኢትዮጵያዊያን ሣይንቲስቶች ከፈረንሣይ አቻዎቻቸው ጋር የአርኪዎሎጂ ጥናት ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ በአርኪኦሎጂ ዙሪያ የተደጉት ጥልቅ ጥናቶች ከጥናቱ የሚኙትን የአርኪኦሎጂ ውጤቶችን በሙዚየም ለማከማቸትና ለእይታ ለማቅረብ ሙዚየሙን መገንባት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በ1944 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ ሙዚየሙ ሲመሰረት ጥቂት ቅሪቶችን በማሰባሰብና ስለአገሪቱ ብሔረሰቦች ክብረ በዓላት የሚያንፀባርቁ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ነበር፡፡ ሙዚየሙ በጊዜ ሂደት እየተሻሻለ እያደገ ሄደ፡፡ በዚህ ሂደትም ውስጥ ሙዚየሙ አሁን ያለበትን ሕንፃ ለመገንባት በቅቷል፡፡
 

 

ሙዚየሙ በአራት ክፍሎች የተከፋፈለ ነው፡-

  • የመጀመሪያው ክፍል ስለሰው ልጅ አመጣጥ ቅድመ ታሪክ የሚያሣይ ሲሆን በዚህ ክፍል የሉሲ አጽምና ቀደምት የሰው ልጆች የሚጠቀሙባቸው የድንጋይ መሣሪያዎችን ይዟል፡፡
  • በሁለተኛው ክፍል ታሪካዊና አርኪኦሎጂካዊ ግኝቶች የሚገኙበት ሲሆን በዚህ ክፍል ከአክሱም በፊት እስከ 16 ክ/ዘመን ያለውን ገጽታ ያሣያል፡፡
  • በሶስተኛው ክፍል የብሔር ብሔረስቦችን ባህልና የክብረ በዓላት ሥርዓት፣ ጊጣጌጦች የሚንፀባረቁበትና የብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚታይበት ነው፡፡
  • በአራተኛው ክፍል ዘመናዊ የሥነ ስዕል ጥበብ ሲገኝ በሥሩም በተለያዩ ኢትዮጵያውያን የተሣሉና የተቀረፁ ሥዕልና ቅርሳ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡


ሙዚየሙ ለጐብኚዎች ምቹ ነው፡፡ ምክንያቱም በእያንዳንዱ ቅርስ /እቃ ላይ ስለእቃው ዝርዝር መረጃ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሙዚየሙ ከመደበኛው ሥራው በተጨማሪ ሙዚየሙን ለመጐብኘት ለሚፈልጉ ተማሪዎችና ጐብኚዎች ልዩ የጉብኝት ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ ሌላው በሙዚየሙ የሚሰጠው አገልግሎት ቱሪስቶች የሚገዟቸውን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ እንዳይወጣ ይከላከላል፣ ይቆጣጠራል፣ በቅርሶች ላይ ፍተሻ ያደርጋል፡፡

አድራሻ፡- አምስት ኪሎከብሉቶፕ ሬስቶራንት ፊት ለፊት
ስ.ቁ፡- +251.11 111 9131/ ext 715ዐ
የጉብኝት ሰዓት፡- ከሰኞ - እሁድ /ከሕዝብ በዓላት በስተቀር/ ከ2፡3ዐ - 11፡3ዐ ሰዓት

ወደ ዝርዝር ማውጫ

የእንጦጦ ሙዚየም

Entoto ከባህር ጠለል በላይ 3ዐዐዐ ሺ ሜትር ላይ በሚገኘው የእንጦጦ ተራራ ዳግማዊ ምኒልክ አዲስ አበባን መስረተዋል፡፡ በዚህ ሥፍራ የንጉሱ ቤተመንግሥት ይገኛል፡፡ ይህ ቤተመንግሥት ከተማዋን ታኮ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ለጐብኚዎች አመቺ የሆነ የትራንስፖርት መንገድ አለው፡፡ በትራንስፖርት መጠቀም ያልፈለጉ ጐብኚዎች መንገዱ አመቺ በመሆኑ ወደሥፍራው በእግራቸው በቀላሉ መድረስ ይችላሉ፡፡ ወደሥፍራውም ሲደርሱ በአካባቢው በሚገኙ ዛፎችና አበቦች ውበትና በአካባቢው ያለው ነፋሻ አየር ይደሰታሉ፡፡ ከዚህም አልፎ የእንጦጦ ሙዚየምና በውስጡ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁና ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ውድ ቅርሶች ይጐበኛሉ፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ ከሚገኙ ታሪካዊ ክርሶች ወደ አድዋ ጦርነት ክተት ሲታወጅ ሲጐሰም የነበረው ነጋሪት፣ አፄ ምኒልክ አንኮበር በነበሩበት ወቅት ሲጠቀሙበት የነበረው አልጋ፣ የአፄ ምኒልክ ዘውድ፣ አፄ ምኒልክ የሚጠቀሙበት የፔርሺያን ምንጣፍ ይገኛሉ፡፡ ከሙዚየሙ አንፃር ዓይንን የሚስበው በአፄ ምኒልክ የተገነቡት የቅዱስ ራጉኤልና የቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት፣ የአፄ ምኒልክ የቀድሞ ቤተመንግሥት ፀለሎች ሊጐበኙ የሚባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

አድራሻ፡ በእንጦጦ ቅድስት ማርያም ቤ/ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ
ስ.ቁ፡ +251.11 666 ዐ465/6/7

ወደ ዝርዝር ማውጫ

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም

IES Museuemየኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በ1963 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ምርምር ተቋሙ ሲቋቋም ሶስት ዓላማዎችን ለማሳካት ታስቦ ነው፡፡ እነዚህም ምርምርና ሥርፀትን ለማከናወን፣ የህትመት ማዕከል ለመሆንና የአገሪቱን ቋንቋ ባህልና ታሪክ ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቀደምትነት ሥልጣኔና የሰው ልጅ መገኛ እንደመሆኗ መጠን ሙዚየሙ የብሔር ብሔረሰቦችን ቱባ ባህል በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ሙዚየሙ ጥንታዊ ቅርሶችን የያዙ ሲሆን ይህንንም በዘላቂነት ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ራዕይን አንግቧል፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የኢትኖግራፊክ ሙዚየም በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች ባህልን በአንድ ጣራ ሥር አካቶ የያዘ ተቋም ነው፡፡ ሙዚየሙ በመግቢያው ላይ በአገሪቱ የሚኙ ብሔር ብሔረሰቦች ህይወትን ከውልድት እስከሞት አልፎም ከሞት ወዲያ እንዴት እንደሚመከቱት ያሣያል፡፡ የመጀመሪያው ፎቅ ላይ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን አልጋንና የኢትኖግራፊክን ክፍል ሲያኙ በሁለተኛው ፎቅ ላይ የአገሪቱን የእደ ጥበብ ውጤቶች ያገኛሉ፡፡ በመጀመሪያ ፎቅ ላይ የሚገኘውንና ንጉሡ ለ1ዐ ዓመታት የተገለገሉበትን አልጋ በተመለከተ አልጋው በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ያለችበትን የሥልጣኔ ደረጃ የአገሪቱ ቤተመንግሥት በወቅቱ በአውሮፓ ከነበሩት ቤተመንግሥታት ጋር ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው ያሣያል፡፡ ወደኢትኖግራፊክ ክፍል ሲያመሩ በአገሪቱ የሚኙ ከ8ዐ የሚበልጡ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገለገሉባቸውን እቃዎች ያኛሉ፡፡ ይህ ክፍል በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው የአገሪቱን የሶሻልና ኢኮኖሚ አጠቃላይ ገጽታ የሚያሣይ በተጨማሪም የብሔር ብሔረሰቦች የማምረቻ መሣሪያዎችና የእደ ጥበብ ቴክኒኮችን ያሣያል፡፡ የሁለተኛው ክፍል ኢትዮጵያን በአጭሩ ያሳይዎታል፡፡ በዚህ ክፍል ከአገሪቱ ክልሎች የተሰባሰቡ የተለያዩ እቃዎችን ያገኛሉ፡፡

በሙዚየሙ በሚኘው ሁለተኛ ፎቅ ላይ የአገሪቱ የሥነ ሥዕል ጥበብ ይመለከታሉ፡፡ በዚህ ክፍል የኢትዮጵያን መንፈሣዊና አለማዊ ገጽታን በሥነ ሥዕል ጥበብ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ክፍል በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የተሣሉ አንዳንድ ስዕሎችን እናገኛለን፡፡

አድራሻ፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ቅጥር ግቢ
ስ.ቁ፡- +251.11 123 9739/ ext 715ዐ
የጉብኝት ሰዓት፡- /ከበዓላት በስተቀር/ ከሰኞ - አርብ ከ2፡0ዐ - 11፡0ዐ ሰዓት
ቅዳሜና እሁድ ከ3፡ዐዐ - 11፡ዐዐ ሰዓት

ወደ ዝርዝር ማውጫ

ዚኦሎጂካል የተፈጥሮ ታሪክ ሙዝየም (ZNHM)

Natural Science Museuemኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት ካላቸው ሃገራት ውስጥ አንድ በመሆንዋ ነው፡፡ አብዛኞቹ የዱር እንስሳት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- 30 የአጥቢ እንስሳት ፣ 28 የወፎች፣ 30 በየብስና በውሃ የሚኖሩ የእንስሳት (amphibians) እና 10% የዓሳ ዝያዎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ተረጋግጠዋል፡፡

ZNHM በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ  በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ  የዱር አራዊት ዝርያዎች ይዞ የሚገኝ ሙዝየም ነው፡፡ ሙዝየሙ ከ1,100 በላይ ዝርያዎች የሳምፕል ስብስቦች አሉት፡፡

ወደ ዝርዝር ማውጫ

 

ባዕታ ሙዝየም

ታአካ ንግስተ ባዕታ ማርያም ቤተ ክርስትያን በቀላሉ ባዕታ ተብሎም ይጠራል፡፡ ከዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ወደ ግራ የሚገኝ ሆኖ 2400 ካሬ ሜትርም ስፋት አለው፡፡ የቤተ ክርስትያኑ ቅጥር ግቢም በትላልቅ ባህር ዛፎች ደን የተሞላ ነው፡፡ ቤተ ክርስትያኑ አራት ማዕዘን ሆኖ ሁለት ታሪካዊ የሆኑ ህንጻዎች ሲኖሩት እነዚህም ህንጻዎች ውድ ከሆነ ድንጋይ የተሰሩ ናቸው፡፡ በነዚህ ህንጻዎች ስር ዳግማዊ ምኒሊክ፣ እቴጌ ጣይቱና ንግስት ዘውዲቱ መቃብር ይገኛል፡፡

የዳግማዊ ምኒሊክ ልጅ ንግስት ዘውዲቱ 1903 ዓ/ም እንዲገነባ አዘዙ፡፡ በተጨማሪም እንደ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ እንዲያገለግልም አደረጉ፡፡
ቱሪስቶች ይህንን ህንጻ (ቤተ ክርስትያን) የሚጎበኙት ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን በህንጻው ወስጥ ያለውን ሙዝየም ለመጉብኘትም ጭምር ነው፡፡ ህንጻው አስራ ሁለት በሮች አሉት፡፡ በስምንተኛም በር መግብያ ላይ በጣም ለዓይን የሚማርክ ከአልሙኒየም የተሰራ የአምበሳ ቅርፅ ይገኛል፡፡

በሙዝየሙ ውስጥ ልዩልዩ፣ የማይረሱና ዋና ዋና የኢትዮጵያ ታሪኮችን የሚያሳዩ ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በታዋቂው አርቲስት አለቃ መዝሙር የተሳሉ ናቸው፡፡
ሙዝየሙ ልዩልዩ ታሪካዊ የሆኑ ፅሑፎች እና ቅርሶች አሉት፡፡ ከነዚህም ዳግማዊ ሚኒሊክ ሲያስቀድሱ  ይቀመጡበት የነበሩ ወንበር የፅሑፍ ታሪክ፣ የአሌክስንደሩ አቡነኬርሎስ የወርቅ መስቀል፣ የንግስት ዘውዲቱ የወርቅ መቋምያ እና የፈረንሳዮ ፕሬዜዳንት የላከው ከቆርቆሮ የተሰራ የክብር ቅጠልና የዳግማዊ ምኒሊክን ሞት ሀዘን የሚገልጹ ናቸው፡፡
 ሌላው ታሪካዊ የሆነው ቤተክርስትያን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ነው ፡፡ ይህንን ቤተክርስትያን መጀመርያ ግቢ ገብርኤል ተብሎ የጠራ ነበር፡፡  ከባዕታ  በደቡብ ምስራቅም ይገኛል፡፡

ወደ ዝርዝር ማውጫ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሙዝየም

ሙዝየሙ በአዲስ አበባ መስተዳድር ህንጻ ፊት ለፊት ገነተጽጌ ቅዱስ ጊዎርጊስ ቤተ ክርስርቲያን ይገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ አመሰራረት ከአድዋ ጦርነት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት እንደ ረዳትና  አዳኝ አድርገው በመቁጠር  በጣልያኖች ላይ ለተቀዳጁት አስደናቂ ድል  ወደ መዲናዋ ሲመለሱ ቤተክርስቲያን እንዲሰራ  አዝዙ፡፡ በ1920ዎቹ መጀመሪያ አጼ ኃ/ስላሴ ቤተክርስቲያኑን እንደገና ሰርተውታል፡፡ የውስጡ የግድግዳ ስዕሎች ደግሞ በአለም ሎሬት አርቲትስ  በአፈወርቅ ተክሌ ተስለዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1990 በቤተ ክርስቲያኗ የደወል ቤት ውስጥ ቋሚ የሆነ ሙዚየም ተከፍቷል፡፡ ሙዚየሙ የተከፈተበት ዋነኛ አላማም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅርሶችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ነው፡፡
በሙዝየሙ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚገልፁ ቅርሶች፣ የነገስታት አልባሳት፣ ዘውድ፣ በትረስልጣን፣ የተለያዩ ቅዱሳት መጻህፍትና ንዋየ ቅዱሳት ይገኛሉ፡፡ቅርሶቹ ስለ ኢትዮጵያ፣ ታሪክ፣ በህግ ክርስትና ሀይማኖት እንዴት በሀገሪቱ እንደተዋወቀና እንደተስፋፋ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ሙዚየሙ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና ለተመራማሪዎች (ለታሪክ አጥኚዎች ትልቅ እገዛ ይሰጣል፡፡

ወደ ዝርዝር ማውጫ


አዲስ አበባ ሙዝየም

የአዲስ አበባ ሙዚየም ዕድሳት ከተደረገለት በኋላ.አዲስ አበባ ሙዝየም ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፓርት መንገድ ኢትዮጵያ ንግድ ማሕበር ሕንጻ ጀርባ ይገኛል፡፡ ሙዝየሙ  የአዲስ አበባ ከተማ እንደ መዲና ሆና የተመሰረተችበትን ምክንያት በማድረግ በ1978ዓ.ም  የተቋቋመ ነው፡፡

የተመሰረተበት ዋነኛ ዓላማም ከተማዋ ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ታሪካዊ ቅርሶች ለመሰብሰብና ለማሳየት፣  የመዲናዋን ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች ለመመዝገብ እንዲሁም ተመራማፈሪዎች ስለ አዲስ አበባ ማጥናት ሲፈልጉ እንደ ዋነኛ መረጃ እንዲጠቀሙበት ታስቦ ነው፡፡  የሕንፃው አሰራር ለየት ያለና ሳቢ በመሆኑ  ለቱሪስቶች ድርብ እርካታም ይሰጣል፡፡

ሙዝየሙ በስምንት የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል ልዩልዩ ቁሳቁስና የከተማዋ የተለያዩ የእድገት ደረጃዎችን ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በፍንፊኔ አዳራሽ የመዲናዋ እድገት በፎቶግራፍ ሲያሳይ በዓድዋ አዳራሽ ደግሞ በአድዋ ጦርነት ተጠቅሞባቸው የነበሩት የጦር መሳሪያዎችን ያሳያል፡፡

ወደ ዝርዝር ማውጫ


የቀድሞው የኢትዩጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ቋሚ አውደ ራዕይ

አውደርዕዩ (Exhibition) ከተራ ፎቶ ግራፍና ከፅሑፍ ሃሳቦች ለየት ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ጉብኚዎች ትክክለኛው የሰው ዘር ከተፈጠረበት ወቅት አንስቶ እስከ አሁን ጊዜ የነበሩትን የተለያዩ ታዋቂ የሆኑ ቅርፃ ቅርፆች እንዲያመለክት በጉበኚዎች እይታ መሰረት እንደሚከተለው ተደልድለዋል፡-

  • የዋሻ ቅድመ ታሪክ ትርጉም (an interpretation of a pre historic cave)
  • የአክሱማዊት ቤተመንግስት ክፍል (A room of an Axumite palace)
  • የላሊበላ ቤተ ክርስትያን ክፍል(A portion of a Lalibela Church)
  • የጉንደር ቤተ መንግስት ቦታ(A Gonder castle area)
  • የሐረር ቤት ማሃል(A Harrar house interior)

በዚህ መልኩ የተደለደለበት ዋነኛ ዓላማም ጉብኚዎቹ ከብዙው በጥቂቱ ጠቅላላ የኢትዮጵያ ገፅታዎች እንዲገነዘቡና በዚህም አስደናቂ ከሆኑት የኢትዮጵያ ባህል፣ ሕዝብና አናኗርዋን ተቋዳሽ እንዲሆኑ፣ስላዩት  ነገር እንዲናገሩ  ተብሎ ነው፡፡

ወደ ዝርዝር ማውጫ

ብርሃን ማዕከል ሙዝየም

የእግረኛ መንገድ ተከትለው ወደ ሰሜን  አቅጣጫ በሚጓዙበት ጊዜ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመው ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ሙዝየምን ያገኛሉ፡፡ብርሃን ማዕከል ከገነት ሆቴል ወደ ቄራዎች ድርጅት በሚወስደው መንገድ ይገኛል፡፡  

ወደ ዝርዝር ማውጫ

ዳግማዊ ምኒሊክ ሚዝየም

በ1903 ዓ.ም በንግስት ዘውዲቱ የተሰራ ሆኖ በዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ ይገኛል፡፡በሙዝየሙ ውስጥ የዳግማዊ ምኒሊክ፣ የንግስት ዘውዲቱ፣ ዳግማዊ ምኒሊክን ያነገሱ ጳጳስ የአቡነ ማቲዎስ፣ የልዑል ፀሃይ እና የአጼ ሃይለስላሴ የልጅ ልጃቸው አፅም ይገኛል፡፡