ቂርቆስ ክፍለ-ከተማ ቂርቆስ ክፍለ-ከተማ

የቂርቆስ ክፍለ-ከተማ አስተዳደር

Kirkos Subcity on Mapየቂርቆስ ክፍለ-ከተማ አስተዳደር ካዛንቺስ ከቶታል ማደያ አለፍ ብሎ በቀድሞ የሸዋ ፖሊስ መምሪያ የነበረ ቢሮ ውስጥ ይገኛል፡፡ የአስተዳደሩ ስልክ ቁጥር 0115-536513 ሲሆን ፋክስ ቁጥሩ ደግሞ 0115-506894 ነው፡፡ በክፍለከተማው ውስጥ 1,598 ቋሚ 117 ኮንትራት ሰራተኞች ይገኛሉ፡፡ በ2003 የበጀት ዓመት 195 ሚሊዮን 679 ሺህ 221 ብር መደበኛ እና 170 ሚሊዮን 395 ሺህ 13 ብር ከ36 ሳንቲም ካፒታል በጀት ለክፍለ-ከተማው ተበጅቶለታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለ7,989 ሰዎች ቋሚና ለ408 ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ክፍለ-ከተማው ውስጥ አራት የመንግስት፣ 38 የግል፣ 14 የህዝብ እና አምስት የተቋም አፀደ-ህፃናት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ዘጠኝ የመንግስት፣ 32 የግል፣ 16 የህዝብ እና አምስት የተቋም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ እየተሳተፉ ናቸው፡፡ ክፍለ-ከተማው አራት የመንግስት፣ አምስት የግል፣ሁለት የህዝብ እና ሶስት የተቋም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገኛም ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ 57 የግልና ሶስት የተቋም ቴክኒክና ትምህርት ስልጠና ተቋማት እንዲሁም አንድ የመንግስት፣ 15 የግል እና አንድ የተቋም ኮሌጆች በክፍለ-ከተማው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሁለት የመንግስት እና አራት የግል ሆስፒታሎች፣ ሶስት የመንግስት ጤና ጣቢዎች፣ 24 ከፍተኛ፣ 18 ልዩ ከፍተኛ፣ ሶስት ልዩ መለስተኛ፣ አስር መካከለኛ እና ስድስት ዝቅተኛ የግል ክሊኒኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰባት መካከለኛ እና 22 ዝቅተኛ የተቋማት ክሊኒኮች፣ ሶስት የግል ዲያግኖስቲክ ላብራቶሪዎችም ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 31 ታሪካዊ ቅርሶች፣29 ፌዴራል መንግሰት መስሪያ ቤቶች፣ 18 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ መስሪያ ቤቶች፣ 11 የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ አስር የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የኢዩ ቤሊዩ ቤተመንግስት፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽህፈት ቤት እና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) መገኛ ነው፡፡ ስምንት ኤምባሲዎች፣ ሁለት መናፈሻዎች፣ 15 ባለ ኮከብና 12 ደረጃቸው ያልታወቀ ሆቴሎች እንዲሁም አራት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ አምስት የእስልምና፣ 16 የፕሮቴስታንት እና ሁለት የካቶሊክ ተቋማት በክፍለ-ከተማው ውስጥ ይገኛሉ፡፡