ፍትህ ጽ/ቤት ፍትህ ጽ/ቤት

የአዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት መልዕክት፤

የአዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የማህበራዊ ፍርድ ቤቶቹን የዳኝነት ሥራ አካሄድ በበላይነት በመምራትና በመከታተል የከተማዉ ነዋሪ በመኖሪያ አካባቢዉ ያለምንም ዉጣ ዉረድ የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ በነዋሪዎች ላይ ሊከተል የሚችለዉን የሀብት ብክነትና መጉላላት ለማስቀረት እንዲሁም ደንብ መተላለፎችን በመከላከል በከተማዉ አስተዳደር ክልል በመቶ አሥራ ስድስቱ ወረዳ ተቋቁመዉ የሚገኙትን ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት በማጠናከር በተሰጣቸዉ የዳኝነት ሥልጣን መሰረት በፍትሐብሔርና በደንብ መተላለፍ /ግምታቸዉ ከብር አምስት ሺህ ያልበለጡ የንብረትና የገንዘብ ክርክሮችን፤ የሀይጂንና የጤና አጠባበቅ ደንብ፤ ከቆሻሻ አያያዝ አሰባሰብና አወጋገድ ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች እንዲሁም ከወንጀል ህጉ ለማህበራዊ ፍርድ ቤት ተለይተዉ የተሰጡ ሀያ ሁለት የደንብ መተላለፍ ድንጋጌዎችን በማየት ከሳሽና ተከሳሽ ጉዳያቸዉን በስምምነት፤ በእርቅ ወይም በሽምግልና እንዲጨርሱ በማድረግ በከተማዉ ነዋሪዎች መካከል ሰላምና መግባባት ተፈጥሮ ጊዜያቸዉንና ገንዘባቸዉን ለልማት እንዲያዉሉ በማድረግ መሰረታዊ የሕግ ትምህርት በማስተማርና በማወያየት ከተማዋ ሰላም፤ ፀጥታና ፍትህ የሰፈነባት እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ከተማ እንድትሆን ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ መደበኛ ፍርድ ቤቶችም ይበልጥ በተወሳሰቡ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ጊዜያቸዉን በማዋል የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ አስችሏል፡፡

በተጨማሪም ጉባኤዉ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸዉን ሲያከናዉኑ ለሚፈጽሙት የሥነ-ምግባር ጉድለት ቅሬታ ተቀብሎ ጉዳዩን በመመርመር የተፈጠረዉን ችግር በመቅረፍ  ረገድ ጉልህ የሆነ ሥራ በመሰራቱ ከሕብረተሰቡ ከፍተኛ ምሥጋና አግኝቷል፡፡

የዳኞች ምልመላን በተመለከተም ነዋሪዉ በዳኝነት ሥራ እንዲሳተፍ በማድረግ ከነዋሪዉ መካከል በታታሪነታቸዉ በታማኝነታቸዉ በሥነ-ምግባራቸዉና በፍትሐዊነታቸዉ መልካም ስም ያተረፉትን በመመልመል በሚያዉቀዉ ሰዉ ሳይሸማቀቅ ሀሳቡን በነጻነት በመግለጽና በማሰረዳት ፍትህን በአካባቢዉ እንዲያገኝ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡