የእሳትና ድነገተኛ አገልግሎት የእሳትና ድነገተኛ አገልግሎት

የስራ አስኪያጁ መልዕክት
    

 የስራ አስኪያጁ መልዕክትየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው በአሁኑ ወቅት ለዘመናት የተከማቹ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ለነዋሪዎቿም ሆነ በከተማዋ ለሚገኙት እንግዶቿ ምቹ የመኖሪያና የስራ ከተማ ለማድረግ በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተመዘገበ ላለው ለውጥም ሆነ ለሚመዘገበው የልማት እድገት የደህንነት ዋስትና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣር ኤጄንሲ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ስለሆነም ኤጄንሲው በከተማው ውስጥ በህይወትና ንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ሰውሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ሰፊ የግንዛቤ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር አደጋ ሲከሰትም ፈጥኖ በመቆጣጠር የነዋሪውን ህይወትና የንብረት ደህንነት እንዲጠበቅ ያድርጋል፡፡

ኤጄንሲው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አደጋን በመከላከል፣ በመቆጣጠር፣ የቅድመ ሆስፒታል ህክምናና የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት የተጣለበትን የሕዝብና የመንግስት አደራ በታማኝነት በመፈፀም ለከተማዋ እድገት ታላቅ አስተዋፅኦ ለማድረግ የከተማውን አስተዳደር የለውጥ እንቅስቃሴ በመከተል በመሰረታዊ አሰራር ሂደት ለውጥ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ቀጣይነት ለማረጋገጥና አገልግሎቱን ለሕዝብ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ሚዛናዊ የስራ አመራርና ውጤት ምዘና ስርአት በመተግበር ከቀድሞው የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ነው፡፡

በተለይም ቅድመ አደጋን የመከላከል ተልእኮ አማራጭ የሌለውና ከፍተኛ ትርጉም ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ከተማዋን ከማናቸውም የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ለመታደግ ከፍተኛ ኃላፍነት የተጣለበት እንደመሆኑ መጠን የአደጋ መንስኤዎችን ህብረተሰቡ አውቆ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ የበኩሉን የመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከተከሰተም በመቆጣጠሩ ሂደት የበኩል ግንባር ቀደም እርምጃ ሊወስድ የሚችልባቸውን ስልቶች በማስገንዘብ የነዋሪውንና የተቋሙን የተቀናጀ ጥረት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እያደረገም ይገኛል፡፡

ለዚህ ስራ ስኬትም የተለያዩ የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች፣ የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የህትመት ውጤቶች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኖችና ልዩ ልዩ የሚዲያ አግባቦችን መጠቀሙ የአገልግሎት አድማሱን ይበልጥ ለማስፋት አስችሎታል፡፡ በአደጋ መከላከል ረገድ ከህብረተሰቡ ጋር ያደረገው ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ ጥረት ያሳደረው የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ በከተማችን የአደጋ መጠን ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ መምጣቱን አመላክቷል፡፡ ይህ ውጤት በስራው ላይ ለተሰማራነው እርካታን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለይ አገልግሎቱን በተመለከተ በጽሁፍ፣ በስልክና በመድረክ እየተሰጡ ያሉት ግብረመልሶች ለቀጣይ ስራችን የሚያበረታቱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ግላዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እስካሉ፣ ተፈጥሮአዊ ተፅእኖዎች/ክስተቶች/ እስካልቀሩ ድረስ አደጋ አይኖርም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ዘመናዊነትን ተከትሎ በሚኖር የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፍሰት፣ የግንባታ ስራዎች መበራከት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ባረጁና ባፈጁ የከተማዋ መኖሪያ ሰፈሮች በርካታ ህዝብ ተፋፍጎና ተጠጋግቶ መኖር ወዘተ. አኳያ በርካታ የአደጋ ስጋቶች በመኖራቸው አሁንም የአደጋ መለከላከል ስራችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ በሁሉም አካባቢ ጥንቃቄን ባሀል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም መዲናችንን ለመለወጥ በምናደርገው የጋራ ጥረት በጋራ አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንነሳ እያልኩ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ሁላችንም ከተማችንን ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የመጠበቅ የዜግነትና ሰብአዊ ግዴታ አለብን!!