ህዳር 29/2011 13ኛው የኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአዲስ አበባ አየተከበረ ነው

 13ኛው የኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ስታዲየም አየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ነው 13ኛው የኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በመከበር ላይ የሚገኘው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበዓሉ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ኢንጂነር ታከለ ለበዓሉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልእክትም እንኳን መዲናችሁ ወደሆነችው አዲስ አበባ እንኳን በሰላም መጣችሁ ብለዋል።

የዛሬዋ ቀን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቃል ኪዳን የሆነው ህገ መንግስት የጸደቀበት በመሆኑም እንኳን አደረሳችሁ ሲሉም ተናግረዋል።

የዘንድሮ በዓል ሀገሪቱ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ ሆና የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኢንጂነር ታከለ፤ በዓሉ ተስፋ የተሰነቀበት ሀገራዊ ለውጡ ወደ አዲስ ምእራፍ የሚሸጋገርበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ አዲስ የለውጥ ምእራፍ እንዲመጣ መሰዋእትነት ለከፈሉት በሙሉ መስጋና ያቀረቡት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ አሁንም ቢሆን ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ስለዚህ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ሀገሬ የሚሏትን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና ነገን አሻግሮ ለማየት የሚያችል ጠንካራ አንድነት በመፍጠር በጋራ መቆም ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ አክለውም የ13ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነት ወደ ታላቅ የሚሸጋገርበት፤ ሀገራዊ ለውጡም ወደማይቀለበስ ደረጃ መድረሱ የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል።

በዓሉ በተሳካ መልኩ እንዲከበር አስተዋፅኦ ለበረከቱ በሙሉም በከተማ አስተዳደሩ እና በራሳቸው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ የታደሙት የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጡበትን አካባቢ ባህል የሚያንፀባርቅ ትርኢትም ያቀርባሉ።

የ13ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታዳሚዎች በሳምነቱ ወደ መዲናዋ የገቡ ሲሆን፥ የበዓሉ አካል የሆኑ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ከነዚህም መካከል የፓናል ውይይት፣ ሲንፖዚየምና ጥናታዊ ጽሁፎች ሲቀርቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

እንዲሁም ባሳለፍነው ሀሙስ 10 ሺህ ሰዎች የተሳፉበት “ኑ ለሰላም ቡና ጠጡ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የቡና ጠጡ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን፥ በእለቱ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በጊዮን ሆቴል የሙዚቃ ድግስ ተካሆዱ ነበር።

በትናንትናው እለትም የ13ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል መርሃ ግብር አካል የሆነ የጎዳና ላይ የሙዚቃ ትርኢት ተካሂዷል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ተወካዮች በብሄር ብሄርሰቦችና ህዝቦች አልባሳትና መዋቢያዎች አጊጠው በብሄራዊ ትያትር አካባቢ በቡድን በቡድን ሆነው በመንገድ ላይ ባህዊ የሚዚቃ ትርኢትና ውዝዋዜዎችን ሲያቀርቡ አምሽተዋል።

                   ምንጭ:-  ኤፍ.ቢ.ሲ


ዜናዎች እና ለውጦች ዜናዎች እና ለውጦች