ህዳር 20 /2011 ምክር ቤቱ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንና የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየ

 የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንና የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ማሻሻያ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፥ ለውጭ ሰላምና ደህንናት እና በተበባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል፡፡

እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው ውይይት አድርጓል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ለውጭ ግንኙንና ሰላም ጉዳዮች እና በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽን እንዲቋቋሙ በመወሰን እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ተከትሎ ነው ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ የተወያየው።

የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምከንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፤ እውነት እና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅን ለማውረድ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ደግሞ በክልሎች የአስተዳደር ወሰንና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮችን ሀገር አቀፍ በሆነ እና በማያዳግም መልኩ ለመፍታት የሚያችል ነው ተብሏል።

እንዲሁም ከወሰን አስተዳደር ጋር ተያይዞ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለው እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆኑንም ተጠቅሷል።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻልና ለማጠቃለል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 2ኛ መደበኛ ስብሳባ ላይ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትና ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አድርጎ ማጽደቁ ይታወሳል።

ሆ0ኖም ግን አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ከተለያዩ አስፈፃሚ አካላት በቀረቡ ጥያቄዎችና በአዋጁ በተደረገው ምልክታ አብዛኛው ከቴክኒክ ችግር የተነሳና የተወሰኑትን የይዘት ለውጥ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች መሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው መሆኑም ተገልጿል።

                     ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ


ዜናዎች እና ለውጦች ዜናዎች እና ለውጦች