ታህሳስ 2/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር የፍራንኮ ቫሉታ አገልግሎትን ማቆሙን አስታወቀ

 የገቢዎች ሚኒስቴር በጠረፍ ላይ ለሚገኙ ዜጎች በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጥ የሚያገኙበትን አገልግሎትን ማቆሙን አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስቴር የፍራንኮ ቫሉታ ለታለመለት አላማ ባለመዋሉ ምክንያት አገልግሎቱን መስጠት ማቆሙን አስታውቋል።

የፍራንኮ ቫሉታ አገልግሎት መቆምን ተከትሎም ጠረፍ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ሸቀጦችን እንዲያገኙ ሌላ መፍትሄ እያመቻቸ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

የፍራንኮ ቫሉታ አላማ ከመሃል ሀገር ለሚርቁና የመሰረተ ልማት ለማይዳረስባቸው ጠረፍ አካባቢ ላሉ ማህበረሰብ  ክፍሎች የእለት ፍጆታ እቃዎች እና ባህላዊ አልባሳት በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ የተፈቀደ ነው።

ይሁን እንጂ በድንበር የጉሙሩክ ስርአትን ተከትለው ከቀረጥ ነጻ የሚገቡት የፍጆታ እቃ ምርቶች ከታለመላቸው አላማ ውጪ መዳረሻቸው መሃል ሀገር በማድረግ የኮንትሮባንድ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ሚኒስቴሩ መግለፁ ይታወሳል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሳለፍነው ሳምንት እንዳስታወቀው፥ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ  2015 እስከ 2018 አጋማሽ ድረስ  በፍራንኮ ቫሉታ ምክንያት ከ14 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ አጥታለች።

መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ ከማጣቱም በላይ ዜጎችን ለመደገፍ ታስቦ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገቡት የፍጆታ እቃዎች ከቀረጥ ነጻ የጉሙሩክ ስርአትን ካለፉ በኋላ  መሀል ሀገር ላይ ከታለመላቸው አላማ ውጪ እየተሸጡ ነው።

የገቢዎች ሚኒስትር  ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከዚህ ቀደም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ መንግስት ስርዓቱ ያለ አግባብ የጥቂት ግለሰቦች መበልፀጊያ ሲሆን ዝም ብሎ እንደማይመለከት መግለፃቸው ይታወሳል።

         ምንጭ:-  ኤፍ.ቢ.ሲ


ዜናዎች እና ለውጦች ዜናዎች እና ለውጦች