Back

ታህሳስ 19/ 2011 ዓ.ም የንግድ ስርዓቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር የከተማ አስተዳደሩ እና የንግዱ ማህበረሰብ በጋራ ሊረባረቡ ይገባል !

አዲስ አበባ የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል ከመሆኗም በላይ የውጭ እና የሃገር ወስጥ ምርቶች የሚሰራጩባት፣ ዋና ዋና ኢንቨስተሮች ፣ አስመጪዎች አከፋፋዮች ጅምላ ነጋዴዎች የሚገኙባት ከተማ እንደመሆኗ በአገራችን የንግድ ሥርዓት ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ተፅእኖ መፍጠር የምትችል ናት፡፡ 
የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የሚካሄደውን የንግዱን ክፍለ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትኩረት በመስጠት ህገ- ወጥነት የተሰራፋባቸውን ዘርፎች በመለየት ከምንጩ ለማድረቅ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡ የንግዱ ኢኮኖሚ ለከተማችን ነዋሪዎች የስራ አድል እና የካፒታል አቅም በመፍጠር ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህን እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ፤ለንግዱ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ 
ይሁን እንጂ በከተማችን የህገ-ወጥ ንግድ አሰራር መኖር በሕገዊ መንገድ የሚነግደውን ነጋዴ በማቀጨጭ በንግድ ዘርፉ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ 
የአዲስ አበባ ከተማ አስዳደር ከመርካቶ እና አከባቢዋ ከተውጣጡ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር በአገራችን ብሎም በከተማችን ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ የንግድ አካባቢ በሚፈጠርበት እና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ በሚመቻችበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። 
በከተማችን እየታየ ያለውን ስር-ነቀል ለውጥ ለማሰቀጠል እና የንግዱን ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ግብር ከፋዩ የለውጡ አካል ሆኖ በከተማችን የልማት እንቅስቃሴ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣበትን ሁኔታዎች ለማመቻችት አስተዳደሩ አና የንግዱ ማህበረሰብ ተቀራርቦ ችግሮችን የሚፈቱበት ስልት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መድረኩ ያመላከተ ነው፡፡

ስለሆነም በንግዱ ዘርፍ በታክስ አሰባሰብ ስርአት ፥ በህገ-ወጥ ንግድ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች ለከተማችን ኢኮኖሚያዊ እድገት አንቅፋቶች በመሆናችው መፍትሄ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሚሠሩ ተግባራት መሆናቸውን አስተዳደሩ በፅኑ ያምናል፡፡

በመሆኑም በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እና የታክስ አሰባሰቡን ዘመናዊ ለማድረግ የከተማችን አስተዳደር ጠንክሮ ይሠራል፡፡ በተለይ ደግሞ የከተማችንን ግብር ከፋይ ችግር መስማት ፥ መደገፍ እና ማብቃት የከተማችንን እድገት ማፋጠን ስለሆነ ፍትሃዊ የንግድ ስርአት ለመፍጠር የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን አስተዳደሩ ተግባራዊ በማድረግ አጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡

ስለሆነም በንግዱ ዘርፍ የሚታየውን ህገ- ወጥነትን ለመከላከልና ስርዓት ለማስያዝ የተጀመረውን ለውጥ እና እንቅስቃሴ አጠናክሮ በማስቀጥል በንግድ እና ግብይት ስርዓት እንዲሁም በግብር ሪፎርሞች ላይ ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት እና የከተማችንን እድገት ለማፋጠን መላው የከተማችን ነዋሪዎች ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን የድርሻችንን እንድንወጣ ሲል ጥሪውን ያቀርባል፡፡ 
               አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሸን ጉዳዮች ቢሮ


የአቋም መግለጫዎች ክምችት የአቋም መግለጫዎች ክምችት