ታህሳስ 1/ 2011 የበጎ ፈቃደኝነትን ባህል ማሳደግ ይገባል- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

የበጎ ፈቃደኝነትን ባህል ማሳደግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበጎ ፈቃደኞች ቀን በማስመልከት ባዘጋጀው መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ለማጎልበት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲዳብር መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝደንቷ፥ ለዚህም ማሳያ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት ወጣቶች በበጎፈቃደኝነት ተደራጅተው ወደ ተለያዩ ክልሎች እንዲሄዱ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የበጎ ፈቃደኝነትን እሴትና ባህል በማጎልበት ለሀገሪቱ ብልጽግና መጠቀም እንደሚገባም ማስስገንዘባቸውንም የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከእያንዳንዱ ዜጋ የምትፈልገው ብዙ ነገር እንዳለ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፥ የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን በማሳደግና እሴቱን በማስፋፋት ለሀገራዊ ልማትና ብልጽግና መረባበረብ ይገባል ብለዋል።

 ምንጭ:-  ኤፍ.ቢ.ሲ

 

ዜናዎች እና ለውጦች ዜናዎች እና ለውጦች