ከንቲባውን ይተዋወቁ ከንቲባውን ይተዋወቁ

Addis Ababa Mayor H.E Driba Kumaከተማችን አዲስ አበባ፤ ሀገራዊ እና አህጉራዊ የመዲናነት ሚናዋን በብቃት ለመወጣት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተመራጭነት ይበልጥ ለማሳደግ በስርነቀል የከተማ ልማት ግስጋሴ ውስጥ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡

የከተማችንን የቀድሞ ጎስቋላ ገፅታ ለመቀየርና ዘመናዊ የከተማ ቅርፅና ይዘት ለማስያዝ፣ በከተማ ማደስና መልሶ ማልማት መስክ እያደረግነው ካለው ርብርብ ጎን ለጎን በመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ፣ በቤቶች ልማትና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ፈርጀ ብዙ የልማት ተግባራት ከተማዋ የምትገኝበትን ፈጣን እድገት አጉልተው የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው፡፡
በእነዚህና በሌሎች በርካታ የልማት መስኮች የተገኙ ውጤቶች፣ ከተማዋ ለኑሮና ለሥራ ተመራጭ እንድትሆን ከማስቻላቸውም ባሻገር ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ትኩረት እንድትስብ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ወደፊትም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶቻችን ሲጠናቀቁ፣ የከተማችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ደረጃ ከፍ እንደሚል እምነታችን የፀና ነው፡፡
 
አዲስ አበባ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ልማት መስክ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሏት ስትራቴጂካዊ ምቹ ሁኔታዎች ያሏት ሲሆን፣ በተለይም የነዋሪዎቿ መልካም የእንግዳ አቀበባልና የመስተንግዶ ባህል፣ የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ እና የነዋሪዎቿ ህብረ-ብሔራዊ ባህል እንዲሁም ዘመናዊ የአየር ትራንስፖርት ማረፊያ የሚገኝባት ከተማ መሆኗ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ከሀገራዊ የመዲናነት ሚናዋ ባሻገር ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የሚካሄዱባት የዲኘሎማሲ ማዕከል እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ከተማዋ አሁን ከደረሰችበት ፈጣን እድገት ጋር የሚመጣጠኑ፣ ደረጃቸውን የጠበቁና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ያገናዘቡ ዘመናዊ የህዝብ መናፈሻ ፓርኮች ከነሙሉ አገልግሎታቸው እንደሚያስፈልጓት እሙን ነው፡፡

ከተማችንን ውብ እና ምቹ የመኖሪያ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ማዕከል ከማድረግ አንፃር አረንዴ ልማት የሚያበረክተውን ጉልህ አስተዋጽኦ በጥልቀት በመገንዘብ፤ የከተማ አስተዳደራችን በአዲሱ የከተማዋ መሪ ፕላን ላይ 30 በመቶ የሚሆነውን ሥፍራ ለህዝብ መናፈሻ ፓርኮችና ለአረንጓዴ ልማት እንዲውል ወስኖ በመንቀሳቀሰ ላይ ሲሆን፤ ይህም አስተዳደሩ ለፓርኮች ልማት ብቻ ሳይሆን ለአካባቢ ጥበቃም ጭምር የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡

በየደረጃው በሚገኙ የከተማዋ አስፈፃሚ አካላት እና የልማቱ ዋነኛ ባለቤት በሆነው የከተማችን ነዋሪ ሰፊ ውይይት የዳበረው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን፤ እንዲሁም ለህብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የከተማ አስተዳደራችን አዲሱ የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናት፤ ከተማችን ዘመናዊ የከተማ ቅርፅና የአስተዳደር ይዘት እንዲኖራት መሰረት እንደሚጥል ይታመናል፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን ቁልፍ የልማት ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ከምናከናውናቸው የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታና በከተማችን ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ከዘረጋነው የቤቶች ልማት ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰር የምናከናውነው የመንገድ አውታር ግንባታ፣ በከተማዋ ምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

የከተማችንን ድርብርብ የመዲናነት ሚና እና ዓለም አቀፋዊ አማራጭ የትራንስፖርት ማዕከልነት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ አዲስ አበባን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እና ዓለም አቀፍ የስብስባ ማዕከል ለማድረግ አስተዳደሩ የተለያዩ ተያያዥ የልማት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ከተማችን በኮንፈረንስ ቱሪዝም ልማት ዘርፍ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ እንድትሆን መልካም ዕድል የሚፈጥርላትን የአዲስ - አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዝቢሽን ማዕከል በባለሃብቱ ተሳትፎ ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በዚህም ሀገራችን በየዕለቱ በበርካታ ሀገራት እንግዶች የምትጎበኝበትን እድል በማስፋት፣ ለሀገራዊ ገፅታ ግንባታ የላቀ ድርሻ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡

በመሆኑም በየደረጃው እየተካሄደ ላለው የለውጥና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሥራዎች ስኬት፤ የሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ በተለይም የልማቱ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የከተማችን ነዋሪ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፤ ለአዲስ አበባ እድገት ከእስካሁኑ በበለጠ በጋራ እንድንረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

አመሠግናለሁ!