ዜናዎችና ለውጦች

በመራጮች ምዝገባ የታየው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በድምጽ መስጫው ዕለትም ሊደገም ይገባል

 በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 26 የምርጫ መርሆዎች መሠረት ማንኛውም ምርጫ ሁሉ አቀፍ፣ ቀጥተኛና በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፍቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት እና ያለምንም ልዩነት በእኩል ህዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በህግ ያልተገደበ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት እንዳለው እያንዳንዱ መራጭ የሚሰጠው ድምጽ እኩል እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን በትግላቸው ያጸደቁት ህገመንግስት ባጎናጸፋቸው ምርጫ ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ባካሄዷቸው አራት አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች የመምረጥና የመመረጥ  ዴሞክራሲያዊ  መብታቸውን በመጠቀም  ወኪሎቻቸውን መርጠዋል፡፡

ህዝቡ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው ምርጫ ወኪሎቹን ለመምረጥ የሚያደርገው  የምርጫ ተሳትፎ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ የመጣ ሲሆን ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በተካሄዱት ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በንቃት በመሳተፍ በዴሞክራሲያዊ መብቱ የመጠቀም ልምዱና በሂደቱም ያለው ዕምነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት  በተካሄዱት ዴሞክራሲያዊ የምርጫ  ተሳትፎዎች ባገኙት ልምድና እየጎለበት በመጣው የዴሞክራሲያዊ ባህል ተጠቅመው የሀገራችንና የመዲናችን  ነዋሪዎች  ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓቱ የሚያደርጉንት ተሳትፎ  አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

በመጪው ግንቦት 16 በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫም  የላቀ የምርጫ ተሳትፎአቸውን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ ፡፡የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ  የታየው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሰየበት ሆኗል፡፡

 በመላ አገሪቱ ላለፉት አርባ ሁለት ቀናት  በአርባ ስድስት ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ ወደ 35 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በምርጫው ለመሳተፍ መመዝገቡና በመዲናችን አዲስ አበባም በአንድ ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚበልጥ መራጭ ተመዝግቦ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱ ይህንኑ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በመራጮች ምዝገባ ወቅት የታየው ከፍተኛ የምርጫ ተሳትፎ የከተማችን ነዋሪዎች ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተጠቅመው ያለምንም ጣልቃ ገብነት  ወኪሎቻቸውን በነጻነት በመምረጥ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥርዓቱ ነጻ፣ሰላማዊ፣ፍትሀዊና  ዴሞክራሲያዊና ሆኖ እንዲቀጥል ያላቸውን የተግባር ዝግጁነት የሚያመለክት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማችን ነዋሪዎች ምርጫው ሰላማዊ፣ነጻ፣ፍትሀዊ፣ዴሞክራሲያዊና በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያሳዩት የነቃ ተሳትፎ እስከ መጨረሻው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ይገልጻል፡፡

በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪ በቅድመ ምርጫው ከፍተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማድረግ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በምዝገባው ያሳየውን   ከፍተኛ ተሳትፎ በድምጽ መስጫው ዕለትም በመድገም በዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠቀም አስተዳደሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡

 

                          የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

 

ማስታወቂያ

የአዲስ አበባ መጽሄት

Showing 1 - 5 of 9 results.
Items per Page 5
of 2

ተዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች